
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ በቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያና የ5 ሚሊዮን ኢትዮ-ኮደርስ የንቅናቄ መድረክ አካሄደ።
በመድረኩ ላይ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ምትኩ አስፋው እንደገለጹት፤ በዲጂታል ዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን ዜጎችን ማሰልጠንና ማብቃት አስፈላጊ በመሆኑ የሀገሪቱን የ2030 ዲጂታል ዕቅድ እውን ለማድረግ በ5 ሚሊዮን ኢትዮ-ኮደርስ የሚሰጠው ስልጠና ዜጎች የዲጂታል እውቀት አግኝተው ተጨማሪ ሥራ እንዲፈጥሩና የኢኮኖሚ አቅማቸው እንዲያድግ ያስችላል።

በአሁኑ ወቅት የመንግሥት አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ እየሆኑ መምጣታቸውን የጠቆሙት አቶ ምትኩ፣ ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ 246 ሺህ 436 ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት መሆናቸውንና በቀጣይ ስድስት ወራት ደግሞ 1 ሚሊዮን 700 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ 110 ሺህ በላይ የኢትዮ-ኮደርስ ሰልጣኞችን ለመመዝገብ ግብ ተጥሎ እስካሁን 28 ሺህ 900 ሰልጣኞች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 7 ሺህ 953 ሰልጣኞችን ሰርትፋይ ማድረግ ተችሏል።
የካፋ ዞን ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታደሰ በበኩላቸው፤ በዞኑ ለ17 ሺህ 200 ሰልጣኞች ስልጠና ለመስጠት ታቅዶ ለ5 ሺህ 200 የሚሆኑት ሰርቲፊኬት ማግኘታቸውን ገልጸው፣ ከዲጂታል መታወቂያ አንጻር ግን ለ711 ሺህ 917 ዜጎች ታቅዶ 140 ሺህ ብቻ በመከናወኑ በቀጣይ ዕቅዱን ለማሳካት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የ5 ሚሊዮን ኢትዮ-ኮደርስ አስተባባሪ አቶ ዋለልኝ ክብረት በበኩላቸው ኮሌጁ ላለፉት ሁለት ዓመታት ስልጠናውን ሲሰጥ መቆየቱንና እስካሁን ከ150 በላይ ሰልጣኞችን ሰርትፋይ ማድረጉን ጠቁመው፣ በቀጣይም በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዳታ ሳይንስና በፕሮግራምንግ ዘርፎች የሚሰጡ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
