
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቴፒ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በክልሉ ለኢንዱስትሪ ልማትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንዳለ በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘመድኩን ሰለሞን ተናግረዋል።
አያይዘዉም በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት ክልሉን ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።


የአምራች ኢንዱስትሪ ድጋፍ በክልሉ የሚገኙ አነስተኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን የመሰረተ ልማትና የግብዓት ችግሮች ለመፍታት ጥረት መደረጉን፣
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ስራዎች ደግሞ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን ማበረታታትና ለክልሉ ምርታማነት የሚያግዙ የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎች ትኩረት ማግኘታቸውን አክለዋል።
በዘርፉ በግማሽ ዓመቱ የታዩ ክፍተቶችን በዝርዝር በመለየት በቀሪዎቹ ስድስት ወራት በተሻለ ፍጥነት ለመስራት መድረኩ ወሳኝ መሆኑንም ሀላፊዉ አስገንዝበዋል።
ይህ በቴፒ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የምክክር መድረክ በዋናነት በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የታቀዱ ግቦችና የተመዘገቡ ተጨባጭ ውጤቶችን ማነፃፀር፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ የአሰራር ጉድለቶችን ማስተካከል፣ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግና የኢንዱስትሪ መንደሮችን ለማጠናከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥም ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢንዱስትሪው ዘርፍ እድገት ለወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የክልላችንን የውስጥ ገቢ ለማሳደግ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
በወቅቱ የተለያዩ መነሻ ሰነዶች ለሚክክር እየቀረቡ ሲሆኑ በጋራ በመምከር የቀጣይ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡ ይጠበቃል።

በመድረኩም የቢሮው አመራሮች፣ የየደረጃው የዘርፉ ባለሙያዎች ከክልሉ 6ቱም ዞኖች የተዉጣጡ ባለድርሻ አካላት የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ ሲል ማሻ ኤፍ ኤም ነው።
